Fana: At a Speed of Life!

የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር ያለመው የኪን ኢትዮጵያና የሀገር ሽማግሌዎች ልዑክ በጎንደር…

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለጥምቀት በዓል አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ ያሸበረቀችው ጎንደር እንግዶቿን እየተቀበለች ነው።

የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን እና በሕዝቦች መካከል አብሮነትን ለማጠናከር ያለመው የኪን ኢትዮጵያ እና የሀገር ሽማግሌዎች ልዑክ በዛሬው ዕለት ጎንደር ገብቷል።

እንግዶች ጎንደር ከተማ ሲደርሱ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ጸጋዬ እና የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አቶ መልካሙ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ኪን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያን እምቅ ብዝሃ ማንነትና ሕብረ ብሄራዊ መገለጫዎች ከማሳወቅ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መተሳሰብ፣ ፍቅርና አንድነት ላይ በትኩረት በመስራት የሕዝቦችን ትስስር ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኪን ኢትዮጵያ ልዑክም በጎንደር ቆይታው የሕዝቦችን ባህል፣ ወግና ልማድ በጠበቀ መልኩ የሕዝቦችን አብሮነትና ትስስር ማጠናከር የሚያስችሉ መርሐ ግብሮችን ያከናውናል።

የኪን ኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር ያለመውን መድረክ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር ነው በትብብር ያዘጋጁት።

ሃላፊው ጥምቀትን በጎንደር ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል።

ጥምቀትን በጎንደር ለመታደም የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የከተማዋ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለእንግዶቹ ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትን ያንጸባረቀ መስተንግዶ ለመስጠት አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት።

ጥምቀትን በጎንደር በተለያዩ መርሐ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን÷ በዛሬው ዕለትም የዚሁ አካል የሆነው የአጼ ቴዎድሮስ ልደት በተለያዩ ኹነቶች ታስቦ ውሏል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.