የሀገራዊ ምክክር መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተቋማት ቁርጠኝነት
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተቋማት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን አሉ።
ኮሚሽኑ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ፣ የትምህርት፣ የጤና ዘርፍ ተቋማት እና ማህበራት እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም ተሳታፊ የሆኑበት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የመድረኩ ዓላማ ኮሚሽኑ የመረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
መድረኩ ከመገናኛ ብዙኃን አማራጮች በተጨማሪ ሕብረተሰቡ በሚገለገልባቸው ቦታዎች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የትራንስፖርት አማራጮች አማካኝነት ኮሚሽኑ ራሱን በሚያስተዋውቅበትና መረጃዎችን ተደራሽ በሚያደርግባቸው መንገዶች ዙሪያ መክሯል።
የመድረኩ ተሳታፊ ተቋማት ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥበት ብቸኛ መንገድ በመሆኑ በተቋማቸው አገልግሎቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ይሳካ ዘንድ በግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከብዝሃ መልዕክት ስርጭት እስከ ሞባይል መተግበሪያ ድረስ ባሉት አማራጮች የኮሚሽኑን መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የሚጠበቅበትን ሀላፊነት እንደሚወጣም ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊ ተቋማት ለኮሚሽኑ መረጃዎች ተደራሽነት በየተቋሞቻቸው ሊያከናውኗቸው የሚችሏቸውን ተግባራት ለይተው ለኮሚሽኑ ያስረከቡ ሲሆን፤ ተግባራቱን በመምራት የሚያስፈፅም የጋራ ግብረ-ኃይልም ተቋቁሞ ሥራ ለመጀመር የሚያስችል ስምምነት መደረጉን ኮሚሽኑ ገልጿል።