በበቂ ሁኔታ ባለመመልከታችን ለዘመናት ከመዲናዋ ልናደንቅ የሚገባንን ውበት ሳናይ ኖረናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበቂ ሁኔታ መመልከት ባለመቻላችን ለዘመናት ከአዲስ አበባ ልናይ የሚገባንን ውበት ሳናይ ኖረናል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክትን በዛሬው ዕለት መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ አዲስ አበባ ከዚህ በላይ እምቅ አቅም አላት፤ ብዙ መሰራት የሚገባቸው እና መታየት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ ብለዋል፡፡
በበቂ ሁኔታ መመልከት ባለመቻላችን ለዘመናት ከከተማችን ልናይ የሚገባንን ውበት ማየት ሳንችል ኖረናል ነው ያሉት፡፡
ቀበና አሁን ያለውን መልክ እና ውበት ሊይዝ ይችላል ብሎ አስቀድሞ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ማየት ሲቻል ስራ ይከተላል ብለዋል፡፡
መደመር ሒደት መሆኑን ገልጸው ÷ ገንዘብን፣ እውቀትን፣ ጉልበትን፣ ሀሳብን እና የአመራር ብቃትን ስንደምር የሚመጣው ውጤት ያማረ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
አሁንም ስንደመር፣ ስንሰናሰል እና ስንደጋገፍ ከዚህ የላቀ ነገር ማድረግ እንችላለን ሲሉም አውስተዋል፡፡
ቀበና እና አካባቢው በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት ከበፊቱ አሁን መሻሻሉን ጠቁመው÷ ልጆቻችን ከዚህ ከፍ አድርገው ይሰራሉ የሚል እምነት እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ