Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ በዛሬው ዕለት በሃድያ ዞን ተጀምሯል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ሱሩር እና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የአፈር ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ሚናው ጉልህ ነው።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዱና የተራቆቱ ቦታዎች እንዲያገግሙ በማድረግ ሥነ ምሕዳርን መጠበቅ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ሕዝብ በተጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው ፥ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የመሬት ለምነትንና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ያግዛል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በንቅናቄው 290 ሺህ 545 ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ነው ያስረዱት፡፡

ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው 1 ሺህ 294 ተፋሰሶች መለየታቸውን ጠቁመው ÷ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው በንቃት እንዲሳተፍ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ለግብርና ባለሙያዎችና ለቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና መሰጡን ነው የገለጹት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.