Fana: At a Speed of Life!

በባሮ ወንዝ ለስድስት ቀናት በልዩ ድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል …

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጋምቤላ አንዷ ናት፡፡

በከተማዋ ባሮ ወንዝ ላይ በጋምቤላና አካባቢው በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው ጥምቀት ትልቅ ሐይማኖታዊ በዓል ነው፡፡

በወንዙ ላይ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በድምቀት መከበሩ ደግሞ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

የቄለም ወለጋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ፣ የጋምቤላና ደቡብ ሱዳን አሕጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር አካባቢውን በማጽዳትና የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ከጥር አንድ ጀምሮ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

በከተራ ዕለት በአካባቢው የሚገኙ 44 ታቦታት ወደ ባሮ ወንዝ ወርደው እንደሚያድሩ የገለጹት ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል÷ በዕለቱ የተለያዩ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

በጥምቀት ዕለት ጠዋት ላይ በርካታ ምዕመናን በባሮ ወንዝ በመገኘት ፀበል የመረጨትና የተለያዩ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ከተከናወኑ በኋላ ቆየት ብለው የቅዱስ ገብርኤል እና ኪዳነ ምህረት ታቦታት ከተደራቢ ጽላቶች ወደ ደብራቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

በማግስቱ የቃና ዘገሊላ ቅዱስ ሚካኤልና ተደራቢ ታቦታት ወደ ደብራቸው እንደሚመለሱ እንዲሁም በጥር 13 ቅዱስ ሩፋኤል እና እግዚአብሔር አብ ከተደራቢ ጽላቶች ጋር እንደሚገቡ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአራተኛው ቀን የአቡነ አረጋዊ ደብረ ዳሞ ገዳም ተደራቢ ጽላቶች ወደ ደብራቸው ይመለሳሉ በማለት ገልጸው÷ በአምስተኛው ቀን የቂርቆስ ዓመታዊ በዓል ተከብሮ ወደ ደብሩ እንደሚመለስ አስረድተዋል።

በየዕለቱም ታቦታትን የመሸኘት መርሐ ግብር ከተከናወነ በኋላ በታቦታት ማደሪያ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ ትምህርታዊ ጉባኤ እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህም ቃለ እግዚአብሔር ይነገራል፣ ማሕሌት ይቆማል፣ ቅዳሴ ይቀደሳል፣ የተለያዩ ዝማሬዎችና ምሥጋናን ጨምሮ የተለያዩ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ይከናወናሉ ብለዋል።

በጋምቤላ ክልል ህዝቦች በተጨማሪ በበዓሉ ላይ ለመታደም ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ እንግዶች እና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በብዛት መገኘታቸው የጥምቀት በዓልን ይበልጥ እንደሚያደምቅ ተናግረዋል።

በዓሉ ሰላምና አንድነት የሚሰበክበት በመሆኑ ሁሉም የእምነቱ ተከታይ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በመጸለይ እንዲሁም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በመወጣትና እርስ በርስ በመደጋገፍ በዓሉን እንዲያከብር አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.