ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር በመገንባት ዘላቂ የገቢ እድገትን የማረጋገጥ ስራዎች ተከናውነዋል – ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ከለውጡ ወዲህ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን በማሳደግና ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመገንባት ዘላቂ የገቢ እድገትን የማረጋገጥ ስራዎች ተከናውነዋል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እመርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ ተገኝተው በገቢዎች ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ፥ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ዘመናዊ የግብር ስርዓትን ለመዘርጋት ተሰርቷል ብለዋል።
በ2011 በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ታክስ በማሳወቅ ረገድ 10 ነጥብ 1 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰው፥ በ2017 ዓ.ም 94 በመቶ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አሳውቀዋል ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ግብር የከፈሉ የግብር ከፋዮች ቁጥር በ2011 ከነበረበት ዝቅተኛ ደረጃ በ2017 ወደ 64 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ256 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በ2018 በጠቅላላው 2 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ዘመናዊ የግብር ስርዓትን በማጠናከር ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠትና የታክስ ተደራሽነትን የማስፋት ጅምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም ቴክኖሎጂ መር የታክስ አስተዳደርን በማስፋት የታክስ ስወራን የመከላከል እንዲሁም በግብር ከፋዩና በታክስ አስተዳደሩ መካከል መተማመን ላይ የተመሰረተ የታክስ ስርዓትን ለመከተል የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት፡፡