ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ የዘመናት የመከራና ጉስቁልና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል – አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን የሰላም አማራጭን በተደጋጋሚ በመግፋት የትግራይ ሕዝብ የዘመናት የመከራና ጉስቁልና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል አሉ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)።
ከተመሠረተበት ማግስት ጀምሮ ችግሮችን በጠመንጃ ለመፍታት የሚሞክር ግትር አቋም ያለው ይህ የወንጀለኞች ስብስብ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሲፈጥር መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ የፖለቲካ አማራጮችን በመዝጋትና ከሻዕቢያ ጋር ያልተቀደሰ ጥምረት መፍጠሩን የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይል ማፍረሱን ጠቁመዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ የፈጠረውን እፎይታ በማደናቀፍ ቡድኑ የሰላም ፀርና የሕዝቡ የጉስቁልና ምንጭ መሆኑን ቀጥሏል ነው ያሉት።
በዚህም ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለስደት፣ ለከፋ ድህነትና ለጭንቀት መዳረጉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የትግራይ ወጣቶችን አግቶ ወደ ጦር ካምፕ ከመውሰድ ጀምሮ፣ ወላጆችን በማሰርና በማንገላታት የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የትግራይ ወጣቶችንና ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው በመንጠቅ ወደ ጦር ካምፕ በማስገባትና ለሻዕቢያና ለሱዳን በመሸጥ የገቢ ምንጭ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉን ሕዝብ ለማዳንና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር፣ የክልሉ ሕዝብ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የቡድኑን የጥፋት ጉዞ ለማስቆም በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራትም የሕገወጡን የሕወሓት እኩይ ተግባር በማጋለጥ የትግራይን ሕዝብ ሊታደጉ ይገባል ማለታቸውን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡