Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል የሚያስችል ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ማንኛውንም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል በጋራ መከላከል የሚያስችላቸውን ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል እንዲሁም ጅቡቲን በመወከል የሀገሪቱ የሰሜን ምዕራብ ግንባር አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሸህሚ ፈርመውታል።

ሌተናል ጀኔራል አሰፋ ቸኮል በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የኢትዮጵያና ጅቡቲ ወታደራዊ ግንኙነት የድንበር አካባቢዎችን ከድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና ታጣቂዎች በጋራ በመከላከል ረገድ የቆየና ታሪካዊ ዳራ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ከአንድ አመት በፊት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ ተገኝተው ወታደራዊ ቅኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፥ በወቅቱ የተጀመረው የትብብር ማዕቀፍ ተጠናክሮ በመቀጠሉ አሁን ለተካሄደው ወታደራዊ ስምምነት ፈር ቀዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ዋና አዛዡ በቀጣይም አዳዲስ ስምምነቶችን በመጨመርና በመከለስ አስፈላጊው ወታደራዊ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በጅቡቲ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ ወልደማርያም በበኩላቸው፥ ሁለቱ ሀገራት በዋና ዋና የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በማተኮር በጋራ እተሰሩ ነው ብለዋል።

ሀገራቱ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች አፈጻጸም ውጤታማ ለማድረግ በቀጣናው የሚገኙ ወታደራዊ አመራሮች የተጠናከረ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዛሬው ውይይትና ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ነው ያሉት፡፡

የጅቡቲ ሰሜን ምዕራብ ግንባር አዛዥ ኮሎኔል አሊ ሸህሚ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት መነሻነት የተደረገው ወይይትና ስምምነት በድንበር ላይ የሚከሰቱ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከልና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በውይይቱ ላይ የጋራ መዋቅር ማቋቋም፣ ወቅታዊና ደህንነቱ የተጠበቀ መረጃ መለዋወጥና ድንበር ተሻጋሪ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መደረሱን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.