Fana: At a Speed of Life!

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር 33 ሚሊየን ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከ33 ሚሊየን በላይ ደርሷል አሉ የብሔራዊ መታወቂያ ባለድርሻ አካላትና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ።

ዳይሬክተሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

አሁን ላይ የተመዝጋቢዎች ቁጥር 33 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመው ÷ ለተቋማት ከ60 ሚሊየን በላይ የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚዎችን የማረጋገጥ ሥራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም የምዝገባ ማሽን ብዛትን 7 ሺህ ማድረስ መቻሉን የገለጹት አቶ ሳሚናስ ÷ በቀጣይ በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራት የተሰሩ ሥራዎች በርካታ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው ÷ በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ ማጭበርበርን ከመከላከል ባለፈ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አብራርተዋል።

በዚህም ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር የባንክ ሒሳብ ቁጥሮችን ከፋይዳ መታወቂያ ጋር የማስተሳሰር ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ በፊት በገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ላይ ላይ የተከናወነው ሥራ ውጤት ማምጣቱንና አሁን ላይ ደግሞ በፋይናንስ ዘርፉ የተጀመረው ሥራ ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር ሚናው ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚከናወነው ሥራ ተጠቃሚዎችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመው÷ ዜጎች ከሀሰተኛ መረጃዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በቀጣይ ተጨማሪ ተቋማትን በፋይዳ ተጠቃሚ የማድረግ፣ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተጀመረውን ሥራ ማጠናቀቅ እና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.