Fana: At a Speed of Life!

የሸበሌ ሪዞርት በዛሬው እለት በይፋ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገበታ ለትውልድ ዋነኛ ፕሮጀክት የሆነው የሸበሌ ሪዞርት በዛሬው እለት በይፋ ተመርቋል።

በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሪዞርቱ÷ በአንድ ጊዜ እስከ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚችሉ ሦስት ምግብ ቤቶች፣ ልዩ የባሕል ማዕከል፣ ዘመናዊ የክብረ በዓላትና የስብሰባ አዳራሾች፣ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎችና 15 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ የእግረኛ መንገዶች መያዙን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።

የሸበሌ ሪዞርት ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ስለመሆኑም አመልክቷል።

10 ሺህ የፍራፍሬ ተክሎች ካረፉበት የፍራፍሬ ፓርክ ጀምሮ እስከ ዋናው የግመል ፓርክ ድረስ እያንዳንዱ የሪዞርቱ ገጽታ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሐብት የሚያንፀባርቅ እንደሆነም ጠቅሷል።

በ51 የተጠናቀቁ የመኝታ ክፍሎችና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገኙ የቱሪዝም አገልግሎቶች እውን የሆነው ሸበሌ ሪዞርት፤ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ታሪካዊ እጥፋት ነው ሲል ጽሕፈት ቤቱ አብራርቷል።

ይህ ፕሮጀክት ህልምን ወደ እውነት የመለወጥ፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮና የባህል ጸጋዎች መላው ዓለም የሚካፈለው ቅርስ የማድረግ የመደመር መንፈስ በተግባር የታየበት ታላቅ ስራ ነው ብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.