Fana: At a Speed of Life!

የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ከ32 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት 6 ዓመታት ከ32 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ ማልማት ተችሏል አለ የግብርና ሚኒስቴር።

በግብርና ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ይመር ዳውድ እንዳሉት÷ ባለፉት ዓመታት ሰፊ መሬት በተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲለማ የሚያስችል ተግባራት በማከናወን ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ተደርጓል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈርን እርጥበት የመያዝ አቅም እንደሚያሳድግና የኬሚካል ማዳበሪያዎችን ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

የአፈር ለምነትን ለመመለስ የተቀናጀ የኮምፖስት ዝግጅት ስራ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት አሲዳማ መሆኑ መረጋገጡን አንስተው፤ ይህንን ችግር በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው ካሉ የግብርና አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ21 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኖራ መታከሙን አመልክተዋል።

ኮምፖስትና የቨርሚ ኮምፖስት የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን በስፋት በመጠቀም አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርታማነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ እንደሚገኙ ነው ያብራሩት።

ዘላቂ ግብርናን ለማረጋገጥ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና የሀገርን የውጭ ምንዛሪ ጫና ለማቃለል ህብረተሰቡና አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.