ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ቀጣናውን የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን በተግባር አሳይታለች – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ከራሷ አልፈው ቀጣናውን በጋራ ተጠቃሚነት የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን በተግባር አሳይታለች አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፡፡
አገልግሎቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፥ አሁን ላይ በየእለቱ የሚበሰሩ ውጤቶች ኢትዮጵያ ማንኛውንም ውስብስብና ግዙፍ ሥራ የማስተባበርና የመምራት አቅም እንደፈጠረች ማሳያ ናቸው ብሏል።
የጀመርነውን ጨርሰን ለትውልድ የማስተላለፍ ባህል እየተገነባ መምጣቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋን ሰንቋል ሲል በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
“ከሕልም ወደ እውነት፡ ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ብልፅግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል!”
ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስና ብሩህ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ትላንት ስናልማቸው የነበሩ ታላላቅ ርዕዮች ዛሬ በተግባር ተተርጉመው የዜጎች ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባቸው፣ የሀገር ክብር የሚታደስባቸውና የቀጣናው ትስስር የሚጠናከርባቸው ህያው እውነታዎች ሆነዋል።
በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የቀጣናው ሀገራት መሪዎች በተገኙበት የተመረቁት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የመሆን ህልሟን ለማሳካት የያዘችው ጽኑ አቋም ማሳያ ናቸው።
ይህ ታሪካዊ ዕለት ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የታዳሽ ኃይል ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጥበትን የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቱሪዝም ዘርፉንና የባህል እሴቶቻችንን ከፍ የሚያደርገውን የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውን የሸበሌ ሪዞርትን ለዓለም ያስተዋወቀችበት አጋጣሚ ነው።
እነዚህ ተግባራት የመደመር እሳቤ ያዋለዳቸው ከሕልም ወደ እውነት የተሸጋገሩ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክቶችና የምሥራቅ አፍሪካ የጋራ ልማት ዋስትናዎች ናቸው።
ዛሬ በሀገራችን እየታየ ያለው ትልቁ ድል ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው መመረቃቸው ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክት ጀምሮ መጨረስ የዕለት ተዕለት ተግባራችንና መለያችን መሆኑም ጭምር ነው።
ይልቁንም ይበልጥ የሚያስደምመው ሀገሪቱ ከአንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ ሌላ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የምትሸጋገርበት ፍጥነት፣ ቅልጥፍና እና የማላቅ አቅም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ታላላቅ ርዕዮችን አልሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር የመለወጥ ብቃት ያለው ትጉህ አመራርና ከእያንዳንዱ የለውጥ ጉዞ ጎን የተሰለፈ ቆራጥ ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗን በተግባር አስመስክራለች።
በእያንዳንዱ እለት የሚበሰሩ ውጤቶች ኢትዮጵያ ማንኛውንም ውስብስብና ግዙፍ ሥራ የማስተባበርና የመምራት አቅም እንደፈጠረች ማሳያ ናቸው።
የጀመርነውን የመጨረስና የቋጨነውን ደግሞ ለቀጣይ ትውልድ በቅርስነት የማስተላለፍ ባህል በሀገራችን እየተገነባ መምጣቱ ለነገዋ ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋን ሰንቋል።
በእነዚህ ፕሮጀክቶች ምረቃ ላይ የቀጣናችን ሀገራት መሪዎች በጋራ መገኘታቸው ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምታከናውናቸው የልማት ሥራዎች ሁሉ ከራሷ አልፈው ለጎረቤቶቿ የሚተርፉና ቀጠናውን በጋራ ተጠቃሚነት የሚያስተሳስሩ መሆናቸውን በተግባር አሳይታለች።
የአይሻ-2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የንፋስ ኮሪደር ላይ መገንባቱ፣ ኢትዮጵያ የቀጣናው የታዳሽ ኃይል ማዕከል የመሆን ጉዞዋን የሚያፋጥን ታሪካዊ ክስተት ነው።
ይህ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለሀገራችን ኢንዱስትሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናው ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር የጀርባ አጥንት ነው።
በቴክኖሎጂ ለሚመራና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለሚታገዝ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነው ይህ መሰረተ-ልማት፣ በሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት የሚያጠናክር የሰላም ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
ኢትዮጵያ ኃይልን በማመንጨትና ለአጎራባች ሀገራት በማከፋፈል፣ የቀጠናው የኢኮኖሚ ሞተር የመሆን ሚናዋን ቃልን በተግባር በመፈጸም እየተወጣች ትገኛለች።
ሀገራችን ዛሬ ከወንዞቻችን፣ ከንፋስና ከምድር ውስጥ እንፋሎት በምታመነጨው ንጹህ ኃይል በአለም አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት መሪ እየሆነች መጥታለች።
እነዚህ ስራዎች የኃይል ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለዓለም የበካይ ጋዞችን የመከላከል ጉዞ የበኩሏን ጉልህ አስተዋፅኦ ያሳየችበት አውድ ነው።
በተመሳሳይ መልኩ የሸበሌ ሪዞርት ባህላዊ እሴቶቻችንን ከዘመናዊነት ጋር አቀናጅቶ፣ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን ሰፊ አቅም ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመለወጥ ብቃቷን ያሳየበት የ‘ገበታ ለትውልድ’ ድንቅ ውጤት ነው።
በአጠቃላይ ትላንት በሰላም እጦት ይታወቁ የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ የልማት ተምሳሌት መሆናቸው፣ ሀገራችን እየገነባች ያለቸው ሰላም ለልማት ማገር መሆኑን ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ የምታልም ብቻ ሳትሆን ሕልሟን ወደ እውነት የምትቀይር፣ የቀጣናውን የልማት ተስፋ የምታለመልምና የአፍሪካ ኩራት ሆና የምትቀጥል ቆራጥ ሀገር ናት።
ትላንት የተመረቁት ፕሮጀክቶች የነገዋን ብልፅግና የምናረጋግጥባቸው ኩሩ ቅርሶቻችን ናቸው።
መንግሥት ከቀጣናው ሀገራት ጋር በመሆን ለጋራ ብልፅግና የሚተጋበትን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል።
ህዝባችንም ይህንን የታሪክ እጥፋት በአግባቡ በመረዳትና ለላቀ ሥራ በመነሳሳት የሀገራችንን ከፍታ እንዲያረጋግጥ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ በቀጣናው የብልፅግና ጮራ፣ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ሆና መዝለቋን ትቀጥላለች!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት