በኢትዮጵያ ታሪክ አመርቂ የኢኮኖሚ ውጤት ተመዝግቧል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማንኛውም መመዘኛ በሀገሪቱ ታሪክ አመርቂ የኢኮኖሚ ውጤት ተመዝግቧል አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዋነኛ ዓላማዎች የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ማረቅ፣ ግብርና መር የእድገት አቅጣጫን ወደ ብዝሃ ዘርፍና ብዝሃ ተዋናይ የኢኮኖሚ መንገድ መቀየር እንዲሁም የብድር ስርዓትን በማስተካከል የእዳ ጫናን ማቅለል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም በማንኛውም መመዘኛ በማያከራክር ሁኔታ በሀገሪቱ ታሪክ አመርቂ የኢኮኖሚ ውጤት የመጣበት ዘመን ነው ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሀገራዊ እድገት ባሻገር የአፍሪካን ቀጣይ ተስፋ በሚያመላክት አግባብ የተጀመረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ማሻሻያው ዛሬ ባስገኘው ውጤት ብቻ ሳይሆን በወደፊቱ የኢኮኖሚ እድገት ሊመዘን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ባለፈው የፈረንጆቹ 2025 በዓለማችን ፈጣን እድገት ከተመዘገበባቸው 10 ሀገራት አምስቱ አፍሪካ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ይህም ጅምር የኢኮኖሚ ስራዎችን ማጠናከር ከተቻለ ብልጽግናን ወደ አፍሪካ ለማምጣት ሰፊ እድል እንዳለ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም ባንክ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ሪፖርቶች መሰረት ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ነዳጅ ከማያመርቱ ቀዳሚ 10 ሀገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ አቅዳ እየሰራች ሲሆን፥ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትንበያ መሰረት እድገቷ 9 ነጥብ 3 በመቶ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገቡትን ውጤቶች በመገምገም ከዚያ በላይ እድገት ማስመዝገብ ስለሚቻል እቅዱን ወደ 10 ነጥብ 2 ለማሻሻል ሀሳብ መቅረቡን አንስተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ