በወታደራዊ ሳይንስና የአመራር ጥበብ የሰለጠኑ እጩ መኮንኖች ተመረቁ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሜጀር ጀነራል ሀየሎም አርዓያ ወታደራዊ አካዳሚ በወታደራዊ ሳይንስና የአመራር ጥበብ ያሰለጠናቸውን እጩ መኮንኖች በም/መ/አ ማዕረግ ዛሬ አስመርቋል።
ጀነራል ብርሀኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ተመራቂዎች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ህዝብ ወዳድነትና ጀግንነት መላበስ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የባከነባትን ጊዜ አካክሳ እንድትሄድ ፤ የጅመረችውን የልማት ፣ የሰላምና የዲሞክራሲ ጉዞ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ሠራዊቱ ዝግጁ መሆኑን ጀነራል ብርሀኑ ገልፀዋል።
የሜጀር ጀነራል ሀየሎም አርዓያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ሜጀር ጀነራል ታደስ መኩሪያ በበኩላቸው÷ ተመራቂዎች ለ13ኛ ጊዜ የመደበኛ ዕጩ መኮንነት ትምህርትና ስልጠና ለሁለት ዓመት ወስደው በማጠናቀቅ ፣ በወታደራዊ ሳይንስና የእመራር ጥበብ በዲግሪና በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ መመረቃቸውን ማረጋገጣቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በስነ ስርዓቱ ላይ የሆለታ ከተማ አስተዳደር ፣ ጀነራል መኮንኖች ፣ የሰራዊት አባላት ፣ የተመራቂ ቤተሰቦች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።