የወንጌል አማኞች ለሀገር ሰላም እና እድገት እንዲተባበሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል የወንጌል አማኞች ለሀገር ሰላም እና እድገት ሊተባበሩ ይገባል አለ፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል 5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል።
የካውንስሉ ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ እንዳሉት፤ ካውንስሉ በሀገር ሰላም ግንባታ ስራ ከሌሎች የሀይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡
በማሕበራዊ እና ልማታዊ ስራዎች ከቤተክርስቲያን የሚጠበቀውን ስራ ለማከናወን ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የወንጌል አማኞች ለሀገር ሰላም እና እድገት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበው፤ ትውልዱ ሰላማዊ እና በጎ ተጽዕኖ ያለው እንዲሆን አባላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ካውንስሉ እንደሌሎች የሀይማኖት ተቋማት በአዋጅ እንዲቋቋም በማድረጉ መንግሥትን አመስግነዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ አምባሳደር እሸቱ ደሴ በበኩላቸው ለሕዝብ ሰላም እና እድገት የኃይማኖት ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።
የሀይማኖት ተቋማይ ለሀገር ግንባታ እና ሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንግሥት ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዮናስ ጌትነት