የህዝቡን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰላምን የማጽናት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ ደስታ ሌዳሞ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰላምን የማጽናት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ።
7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ የፌደራልና የክልሉን የጸጥታ ተቋማት ያቀፈ የፀጥታ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ ሕብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰሩ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች ውጤት ተገኝቷል።
በክልሉና በአጎራባች አካባቢዎች ሰላምን ለማጽናት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የማጠናከር ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ በዚህም አልፎ አልፎ ይከሰት የነበረውን ግጭት ማስቀረት ተችሏል ነው ያሉት።
የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን የማጽናት ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የጸጥታ ግብረ ሃይሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት ለዘላቂ መፍትሄ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የክልሉ መንግስት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ግብረ ሃይሉ በክልሉና አጎራባች አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ የማፅናት ስራ እንደሚሰራ የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡