Fana: At a Speed of Life!

አህጉራዊ አቅም የሆነው የአፍሪካ ህብረት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ህብረት የአህጉሩን 55 ሀገራት በአባልነት ያቀፈ ግዙፍ አህጉራዊ ተቋም ነው።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሚለው ስያሜ ለ39 ዓመታት የቆየው ይህ ተቋም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሚለውን ስያሜ ይዞ አህጉራዊ አንድነትን ለማጠናከርና የፓን አፍሪካኒዝም ራዕዮችን እውን ለማድረግ መስራት ከጀመረ 24ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።

ነጻነታቸውን የተጎናጸፉ 32 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በፈረንጆቹ 1963 ግንቦት ወር ላይ በአዲስ አበባ ተሰባስበው ነበር።

የስብሰባቸው ዓላማም ከነጻነት በኋላ የአፍሪካን አንድነት፣ ሰላም እና ልማት እውን ለማድረግ የሚሰራ ግዙፍ ተቋም እውን ማድረግ ነበር። በዚህም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተወለደ።

ድርጅቱ የፓንአፍሪካ ራዕይ መገለጫ የሆነውን የተባበረች እና ነጻነቷን ያስከበረች አህጉር ትፈጠር ዘንድ አልሞ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

የህብረቱ መመስረት ከቅኝ ግዛት እና አፓርታይድ ጋር የሚደረገውን ትግል ለመደገፍ፣ የአፍሪካ መንግሥታትን ነፃነት ለመጠበቅ እና በሀገሮች መካከል ያለውን ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነበር።

በኋላም አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ አገዛዝ ስርዓት ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎ የኢኮኖሚ ልማት፣ ሰላም፣ እንዲሁም የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታን ጨምሮ አህጉሪቱ አዳዲስ ፈተናዎችን መጋፈጥ ግግድ ሆኖባታል።

የአፍሪካ መሪዎች እነዚህን ፈተናዎች በተሻለ መልኩ ለመፍታት ያስችላል በማለት በፈረንጆቹ 2002 ሐምሌ ወር ላይ የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት በመለወጥ የአህጉሪቱን ሚና ከፍ ለማድረግ በጋራ መትጋት ጀመሩ።

ህብረቱ አባል ሀገራቱን በመያዝ ሰላምና ደህንነትን፣ የኢኮኖሚ ውህደትን፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን፣ ዲሞክራሲንና የአፍሪካን የጋራ ድምጽ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች በማስተጋባት የተባበረችና የበለጸገች አፍሪካን የረዥም ጊዜ ራዕይ ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

በጥር 23/2007 ዓ.ም “አጀንዳ 2063” እቅድን አፅድቆ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፥ የዚህ አጀንዳ ግብ ሁሉን አቀፍና አካታች ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ውጤታማ የአስተዳደር ስርዓትን በማስፈን አህጉሪቱን ወደ ላቀ ዓለም አቀፋዊ ተዋናይነት ከፍ ማድረግ ነው።

በአዲስ አበባ ዋና መቀመጫውን ያደረገው ህብረቱ የመሪዎች ጉባኤውን በየዓመቱ የሚያካሂድ ሲሆን፥ ዘንድሮም ለ39ኛ ጊዜ በመዲናችን ይካሄዳል፡፡

በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ የአፍሪካ መሪዎች በአህጉሪቱ ልማት ላይ ያተኮሩ የትምህርት፣ ጤና፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም አህጉሪቱ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ፥ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንም ያሳልፋሉ፡፡

ከመሪዎቹ ጉባኤ ቀደም ብሎ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚካሄደው 48ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ የአባል ሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ፡፡

ሚኒስትሮቹ በስብሰባው ላይ ሰፊ ውይይቶችን በማድረግ ለመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የሚያጸድቁ ይሆናል፡፡

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.