የኮይሻ የኃይል ማመንጫ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኃይል ማመንጫ ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተጠናቅቋል፡፡
የፕሮጀክቱ የሲቪል መሐንዲስ ይታገሱ አያሌው እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ከጊቤ-3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቀጥሎ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።
የግድቡ የአርማታ ሙሌት ግንባታ ከመከናወኑ በፊት ከ7 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ ልል አፈር የማንሳት ሥራ መከናወኑን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ7 ነጥብ 725 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የአርማታ ሙሌት ውስጥ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት ተጠናቅቋል ነው ያሉት፡፡
ግንባታውን ለማፋጠን በ2 ፈረቃ ለ24 ሰዓታት እየተሰራ ሲሆን፥ በየወሩ በአማካይ ከ100 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ግድቡ አሁን ላይ ከባህር ጠለል በላይ 623 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን ጠቁመው፥ ይህም የግድቡ ቁመት አሁን ላይ 136 ሜትር እንዲሆን ማስቻሉን አንስተዋል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮንክሪት ሙሌት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 6 ተርባይኖች ያሉት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተከላ ሥራና የሁሉም ተርባይኖች ክፍሎች በምርት ሒደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ግንባታን ለማጠናቀቅ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የልል አፈርና የጠንካራ አለት የቁፋሮ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፥ የስትራክቸራል የአርማታ ሙሌት ሥራውም 45 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በቁፋሮ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ የአለት አካላት ግድቡን በሚገባ መሸከም እንዲችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸው፥ ይህም ወደ ፊት ሀገሪቱ በምታከናውናቸው መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም መስህብነት ከፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል፡፡