Fana: At a Speed of Life!

የውሃ ሃብታችንን በኃላፊነትና በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የውሃ ሃብታችንን በኃላፊነትና በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ ነው አሉ፡፡
39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ አፍሪካውያን የውሃ ሀብት የዕድገት መሰረት መሆኑን በመረዳት በአግባቡ መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በሰራችው ስራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቷን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም አፍሪካውያን የውሃ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በአፍሪካ ዕድገት ከፍ ያለ ተፅዕኖ ማሳደር እንችላለን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት መጨረሻ በ10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፥ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥና የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በከተማና በገጠር ሰው ተኮር ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የገጠሩን ማሕበረሰብ ኑሮ ዘመናዊ ለማድረግ፣ የገበያ ትስስርን ለማስፋትና ንጹህ የመጠጥ ውሃን ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሰራችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል አንጻር ትልቅ ሚና እየተወጣች መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በኮፕ 32 ጉባኤ ላይ አፍሪካ በአንድ ድምጽ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለዓለም ታቀርባለች ነው ያሉት፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.