በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ማዕከል ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አወል ሰይድ (ዶ/ር)በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ ግንባታው ለወሎ ቴርሸሪ ኬር ሆስፒታል ግንባታ ሕብረተሰቡ ቀደም ሲል ባሰባሰበው ገንዘብ የተጀመረ ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ ከሕዝብ የተሰበሰበውን 95 ሚሊየን ብር የተቀበለው ወሎ የኒቨርሲቲ ለሕብረተሰቡ ማስታወሻ እንዲሆን በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግንባታውን እንደጀመረ ተናግረዋል።
ለግንባታው፣ ለማሽኖችና ለተለያዩ ግብዓቶች ማሟያ ከሕዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ላይ በመጨመር 187 ሚሊየን ብር መመደቡን ገልጸው÷ ግንባታውን በ3 ወር በማጠናቀቅ ሥራ ለማስጀመር መታቀዱን ተናግረዋል።
የሚገነባው የኩላሊት እጥበት ማዕከል በአንድ ጊዜ ለ34 ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ እንደሆነም ተነግሯል።
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ሐይማኖት አየለ በበኩላቸው÷ የኩላሊት እጥበት ማዕከል ባለመኖሩ ታካሚዎችን ወደ አዲስ አበባ ሪፈር እንደሚልኩ እና በዚህም ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ወሎ የኒቨርሲቲ ኃላፊነቱን ወስዶ የተሻለ የኩላሊት ማጠቢያ ማዕከል ግንባታ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በከድር መሀመድ