Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ኢትዮጵያ በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኗን ይገነዘባሉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኗን ይገነዘባሉ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በመከባበር፣ በመደጋገፍና አብሮ በመስራት ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ለማጠናከር ከፕሬዚዳንቱ ጋር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን የቀጣናውን ሁኔታ የሚገነዘቡ በመሆናቸው በሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ያደረግነው ውይይት እጅግ ፍሬያማ ነበር ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆኗንና ሚናዋን መወጣት እንዳለባት ያምናሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ረገድ ፕሬዚዳንቱ ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፥ ከፍተኛ እድገት እያስመገበች የምትገኘው አህጉሪቱ በሚቀጥሉት ዓመታት የሚገባትን ቦታ እንድትይዝ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ጥረት ውስጥ በአውሮፓ እና እስያ መካከል ባላት ጉልህ መልክዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚና በአፍሪካ እድገት ውስጥ የበኩሏን ድርሻ እንድትወጣ ተወያይተን ተግባብተናል ነው ያሉት፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.