የወለጋ ልማት የሃሳብ ልዕልናና የአላማ ጽናትን የሚያሳይ ነው – እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የወለጋ አካባቢ ልማት የሃሳብ ልዕልና እና የአላማ ጽናትን የሚያሳይ ነው አሉ።
እዮብ (ዶ/ር) በወለጋ ዞኖች በተደረጉ የልማት ሥራዎች ጉብኝት ዙሪያ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት÷ አካባቢው ሌላ የልማት ምዕራፍ ውስጥ ገብቷል።
የወለጋ ልማት የሃሳብ ልዕልና እና የአላማ ጽናትን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸው÷ የሆነ ጊዜ ላይ ቀጣናው የግጭትና የሰላም እጦት መግለጫ የሚሰጥበት እንደነበርና ዛሬ ላይ ግን የተትረፈረፈ ልማት የሚታይበት እንደሆነ ተናግረዋል።
በሁሉም ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች ከራስ ተርፈው የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኙ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ቤኒሻንጉል አካባቢ ካለው ፕሮጀክት ጋር የሚወዳደር ትልቅ ፕሮጀክት ነው ያሉት እዮብ (ዶ/ር)÷ የለውጡ አመራር የኢትዮጵያን የልማት አቅም ማውጣት አለብን በማለት በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ከገመትነው እና ካሰብነው በላይ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመሆን ትርጉም ያለውን ለውጥ ማምጣት ችሏልም ነው ያሉት።
ነቀምቴ አሁን ተሞሽራለች፤ ወጣቶች ወደ ስራ መግባት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በሶስና አለማየሁ