Fana: At a Speed of Life!

“ህገ ወጡ ህወሓት ይሙት፤ ፍቀዱለት”

የፍርስራሹ ህወሓት ቡድን የጦርነት ዛር ተነስቷል። ደም ካልጠጣ የማይረካው ጨካኝ ስብስብ ምድር ጠባው፤ ሰማይ ካልቧጠጥኩ እያለ ነው።
የትግራይ ክልልን ህዝብና መዋቅር አግቶ ይዞ፤ እልቂት እና ጦርነት ማወጅን የሰርክ ተግባሩ አድርጓል።
የትግራይ ህዝብ ጦርነት በቃኝ፤ ሰላም ይሁን እያለ ተማጽኖውን ቢያሰማም ህገ ወጡ ህወሓት ግን፤ ሰላም እምቢኝ ጦርነት ይሁንልኝ ብሎ እየፏለለ ነዉ።
በመቃብር አፋፍ ላይ ያሉት አረጋዉያን፤ በአፍላ ወጣቶች ሞት ራሳቸዉን ለማኖር ቋምጠዋል። የህገ ወጡ ህወሓት ዘዋሪ እድሜ ጠገብ አዛውንቶች፤ ከአስመራ አቻዎቻቸዉ የቀሰሙት እውቀት ይህንኑ ነው።
በወጣት ሞት መኖር፤ በሰው ደም መነገድ ከሻዕቢያ ጓዶቻቸው የተማሩት ትምህርት ነው፤ ይህ ሁኔታ ዛሬ ላይ የትግራይ እናት ልጇ ከጉያዋ ተነጥቆ ለጦርነት ገበያ ለሽያጭ እንዲቀርብ አስገድዷል።
አሁን የህገ ወጡ ህወሓት ጀምበር ጠልቃለች። ቡድኑ ባጭሩ በዓማፂነት ተወልዶ፤ ወደ መንግሥትነት አድጎ፤ በኋላም፤ ቁልቁል ተመልሶ ዓማፂ ቡድን በመሆን እድሜውን ቋጭቷል።
ይህ ህገ ወጥ ቡድን፤ ዛሬም 1970 እና 1980 ላይ ያለ ይመስለዋል። በጓንዴ፣ ቁመህ ጠብቀኝ እና በሰዉ ማእበል፤ ጦርነትን አሸንፎ ወደ ስልጣን የመመለስ ቅዠት ያባንነዋል።
ቡድኑ፤ ከስልጣን በቀር ህልም፤ ከዝርፊያ ያለፈ ትልም ስሌለው የትግራይ ክልል ህዝብ አንቅሮ ተፍቶታል። ሞታችንን ሙቱልን የተባሉት የትግራይ ወጣቶችም፤ ህይወትና አካላችንን ለእናንት ድሎት እንገብርም የሚል ግልፅ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን ላይ ህገ ወጡ ህወሓት በድዳቸዉ የቀሩ አረጋውያን ስብስብ ነው።
ለትግራይ ህዝብ ሰላም ህይወቱ ሲሆን፤ ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን ደግሞ የፖለቲካ መዋቅርና አስተሳሰቡ በግጭትና በጠላት ፍለጋ ላይ የተገነባ ነው።
በመሆኑም ከጦርነት በላይ ሰላምን ስለሚፈራ ህይወቱን የሚያቆየው በጦርነት ውስጥ ነው። በሰላም መካከል ህይወት የሌለው ህወሓት ትግራይ ሰላም ስትሆን ሞቱ ይፋጠናል።
በትግራይ ህዝብና በህገ ወጡ ህወሓት መካከል ያለው ግብግብም ይኸው ነው። ህዝቡ በሰላም እንኑር ሲል፤ ህገ ወጡ ህወሓት በጦርነት ልኑር የሚል አቋም ይዟል።
ማንም ሰው እንደሚረዳው የህወሓት እብሪት እና ቆሞ ቀርነት፤ የመቃብር አፋፍ ላይ አድርሶታል። አሁን የቀረዉ ትግል ራሱን ችሎ የፖለቲካ ሞት እንዲሞት መርዳት ብቻ ነው።
የትግራይ ህዝብ በትግልና እምቢታ፤ ኢትዮጵያውያን በፅናትና አንድነት፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም በብስለትና ትዕግስት፤ የህገ ወጡን ቡድን “ይዣችሁ ልሙት” ጥሪ እያከሸፉበት ይገኛሉ። መፍትሄውም ይኸው ነው፤ የአብረን እንሙት ነጋሪት የሚጎስመዉ ህገ ወጡ ህወሓት ብቻውን በሰላም እንዲሞት መፍቀድ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.