ለልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት በዓል አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በስኬት ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዕዙ ላለፉት 65 ዓመታት የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ የማይተካ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
በልዩ ልዩ ወታደራዊ ትዕይንቶች ሲከበር የቆየው የምስረታ በዓል የዕዙን የጀግንነት ታሪክ ለወጣቱ ትውልድ ያስተላለፍንበትና አንድነታችንን ያጠናከርንበት ሆኗል ነው ያሉት፡፡
በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ድጋፍ ያደረጉ አካላትን አመስግነው፥ ሠራዊቱ ከሕዝብ ጋር ያለውን ቁርኝት ይበልጥ በማጠናከር ለሀገር ሰላምና ደህንነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፥ የሀገር ኩራት የሆነው የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የምስረታ በዓል የሠራዊቱንና የሕዝቡን አጋርነት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለበዓሉ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፥ ለሠራዊቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ለበዓሉ መሳካት ከፍተኛ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የዕዙ አርማና የምስክር ወረቀት መበርከቱን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።