Fana: At a Speed of Life!

የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ጀግኖች በመሆን ተጨባጭ የለውጥ ምሳሌ እንሆናለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ጀግኖች በመሆን ለዓለም ተጨባጭ የለውጥ ምሳሌ እንሆናለን አሉ።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበዓሉ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዓድዋ ድል በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ በማንም የማትደፈር የነፃነት ሀገር መሆኗን በግልፅ ያሳያል ብለዋል።

ዛሬ የምናከብረው የድል በዓላችን ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው አፍሪካውያን ኩራት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ጀግኖች አያቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው ሀገራቸውን በተባበረ ክንድ አስከብረው ነፃነትን ለኛ እንዳስረከቡን ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ልዩነቶችንን በሰከነ መንገድ በማየትና በሀገራዊ አንድነት ላይ በመግባባት ለኢትዮጵያ መስራት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአንድነት ቆመን የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን እናደርጋለን ያሉት ከንቲባዋ÷ የአዲሱ ዘመን የዓድዋ ጀግኖች በመሆን ለዓለም ተጨባጭ የለውጥ ምሳሌ እንሆናለን ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.