የወጣቶች ስብዕና ማዕከላት በሥነ ምግባርና ክህሎት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወጣቶች ስብዕና ማዕከላት በሥነ ምግባር እና ክህሎት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት ጉልህ ሚና አላቸው አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡
በዘመናዊ መልክ እድሳት የተደረገለትና አዲስ የተገነባ የስፖርት መጫወቻ ሜዳን ያካተተው የአጋሮ ከተማ የወጣቶች ስብዕና ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር )በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ለቀጣይ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እና ለሀገር ብልጽግና የወጣቶችን ስብዕና እና ክህሎት መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡
ለዚህም ወጣቶች በሥነ ምግባር ታንጸውና ተኮትኩተው የሚያድጉባቸው ማዕከላት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የአጋሮ ከተማ የወጣቶች ስብዕና ማዕከል የመንግሥት፣ የማሕበረሰቡና የአጋር አካላት የተቀናጀ ጥረትና የመደመር ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
በከተማዋና አካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በማዕከሉ በአግባቡ እንዲገለገሉና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል፡፡
ወጣቶች በመልካም ስብዕና ታንጸው፣ እውቀትና ክህሎታቸውን በማዳበር ለአካባቢያቸው ብሎም ለሀገር ብልጽግና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ማዕከሉ ዲጂታል ቤተ መጽሐፍት፣ አይ ሲ ቲ፣ የስልጠና አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ ካፍቴሪያና የምክር አገልግሎትን መስጠት የሚያስችሉ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ናዚፍ መሃመድ አሚን በበኩላቸው ÷ በከተማዋ የወጣቶችን ሁለንተናዊ አቅም ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡