የቴሌግራም አካውንትዎ በመረጃ መንታፊዎች እጅ እንዳይወድቅ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ የሚገኘው ቴሌግራም የብዙዎቻችን የንግድ እና የማህበራዊ ግንኙነት ማዕከል ሆኗል።
ነገር ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካላደረግን አካውንታችን በቀላሉ የሳይበር ወንጀለኞች ሰለባ ሊሆን ይችላል።
በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተከሰተ ካለው የአካውንት ጠለፋ ራስዎን ለመጠበቅ በአስቸኳይ ሊተገብሯቸው የሚገቡ የጥንቃቄ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦
👉 ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ (Two-Step Verification)
ይህ በጣም ወሳኙ መከላከያ ነው። ጠላፊዎች የእርስዎን የኤስኤምኤስ (SMS) ኮድ ቢሰርቁ እንኳ እርስዎ የፈጠሩት ተጨማሪ የይለፍ ቃል (Password) ከሌላቸው አካውንትዎን መክፈት አይችሉም።
• እንዴት ይተገበራል? Settings > Privacy and Security > Two-Step Verification ውስጥ በመግባት ጠንካራ የይለፍ ቃል ያስገቡ።
👉 አጠራጣሪ ሊንኮችን አይጫኑ!
“የሽልማት ባለቤት ሆነዋል”፣ “አካውንትዎ ሊዘጋ ስለሆነ በዚህ ሊንክ ያረጋግጡ” ወይም “ከቴሌግራም ዋና መስሪያ ቤት የተላከ መልዕክት” የሚሉ ይዘቶች አብዛኛውን ጊዜ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች ናቸው። ማንኛውንም ሊንክ ከመጫንዎ በፊት ምንጩን በትክክል ያረጋግጡ።
👉 የገቡባቸውን መሳሪያዎች ይቆጣጠሩ (Active Sessions)
አካውንትዎን በሌላ ስልክ ወይም ኮምፒውተር ላይ ተጠቅመው መውጣት (Log out) ረስተው ይሆን? ወይም ሳያውቁት ሌላ ሰው እየተጠቀመበት ይሆን?
🔍ለመፈተሽ፦ Settings > Devices ውስጥ በመግባት የማያውቁት መሳሪያ ካለ Terminate በማድረግ በአስቸኳይ ያስወግዱ።
👉 የግላዊነት ቅንብሮችን ያስተካክሉ #Privacy_Settings
የስልክ ቁጥርዎ፣ የፕሮፋይል ምስልዎ እና የ”Last Seen” ሁኔታዎ ለማያውቁት ሰው እንዳይታይ ማድረግ ከማህበራዊ ምህንድስና ጥቃቶች ይጠብቅዎታል።
መረጃውን ያገኘነው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ነው፡፡