Fana: At a Speed of Life!

ቅሬታ የሚነሱባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በነዋሪዎች ቅሬታ ይነሳባቸው የነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ የኮልፌ 18 ማዞሪያ አውቶቡስ ተራ መሳለሚያ እና አየር ጤና ካራ ወለቴ መንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት በመዲናዋ 140 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልጸው÷ በተለይም ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች በመጓተታቸው ለሕዝቡ የቅሬታ ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።

የወሰን ማስከበር እና መሰል ስራዎችን በመስራት ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አየር ጤና ካራ ወለቴ መንገድ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት እንዲሁም የኮልፌ 18 ማዞሪያ አውቶቡስ ተራ መሳለሚያ በ10 ወራ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የመንገዶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ለነዋሪው እፎይታን የሚሰጥና ከመዲናዋ ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች የሚደረገውን የትራንስፖርት ፍሰት እንደሚያሳልጥ ተናግረዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶች የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የአገልግሎት መስጫ መስመሮችና የአረንጓዴ የልማት ስራዎችን በማካተት ደረጃቸውን ጠብቀው እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አየር ጤና ካራ ወለቴ መንገድ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር ስፋት ሲኖረው÷ የኮልፌ 18 ማዞሪያ አውቶቡስ ተራ መሳለሚያ መንገድ ደግሞ 3 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፋት እንዳለው ተመላክቷል።

በቅድስት አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.