Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የነበራትን ቁመና ዳግም እንድትይዝ በትብብር መቆም ያለብን አሁን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ሀያልነት የሚያረጋግጡ ቅሪቶችን አቧራ አራግፈን የነበረንን ቁመና ዳግም ለመያዝ በትብብር መቆም ያለብን አሁን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን መልካ በሎ ወረዳ በሚገኘው ናሲኦል ዋሻ ያደረጉትን ጉብኝት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጉብኝቱ ኢትዮጵያን አውቀን እንዳልጨረስንና ሀብታችን ተዝቆ እንደማያልቅ የተረዳንበት በመሆኑ ብዙ መማርና ብዙ ማሰስ እንደሚጠበቅ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

ስለሀገራችንና ሀብቶቿ በቂ መረጃ ሳይኖረን ሌሎች በሚነግሩን ተንተርሰን የምናወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የተሟላ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሀብቶችና ስልጣኔዎች የሚያስረዱ የራሷ የሆኑ በቂ መረጃዎችን ለማግኘት እንደሚቸግር ጠቁመው፥ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና ሀገር ወዳድ ዜጎች የሀገሪቱን ሀብት አጥንተው ለህዝቡ ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የነበረውን የጥንት ስልጣኔና እውቀት የሚያመላክቱ ቅሪቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከተፈጥሮ ጋር የነበራቸውን መስተጋብር፣ የተፈጥሮና የታሪክ ሀብቶች መለስ ብሎ ማጥናት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ተፈጥሮ ላይ መስራትና ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ጀግኖች የነበሯት ጥንታዊት ሀገር መሆኗን አውስተው፥ የኢትዮጵያን ትልቅነት ለመሸፈን ቢሞከርም ሊሳካ አልቻለም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሀያልነት የሚያረጋግጡ ቅሪቶች አሁንም መኖራቸውን ገልጸው፥ አቧራውን አራግፎ የነበረንን ቁመና ዳግም ለመያዝ ወደ ውስጣችን በማየት፣ በመደመርና በትብብር መቆም ያለብን አሁን ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በጉብኝታችን ብዙ ተምረናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሌሎችም አካባቢውን ቢጎበኙ ወደ ኋላ መለስ ብለው ራሳቸውን ለመመልከትና እውቀት ለመገብየት እድል ያገኛሉ ብለዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.