ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልፈጥር በዓልን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመጠየቅና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል አለ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት።
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ሸሪፍ የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ መግለጫ በሰጡት መግለጫ÷ በዓሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በሌሎች አካባቢዎች እንደሚከበር ገልጸዋል።
በረመዳን ወር የታየው መንፈሳዊ ጥንካሬ፣ መተባበር እና መደጋገፍ በበዓሉ ዕለትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በጾሙ ወቅት የነበረው የመረዳዳት ባህልን በማጠናከር በተለይም አቅመ ደካሞችንና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ በዓሉን በጋራ ማክበር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ጾም ወቅት ካለው ላይ በማካፈል፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ በረከት ሲያገኝ እንደቆየ ሁሉ የመጠያየቅና የመረዳዳት እሴት ሁልጊዜም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡
በጌታሰው የሽዋስ