Fana: At a Speed of Life!

የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል አለ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፡፡

የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው እስከ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፥ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ17 ሚሊየን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ መታቀዱ ነው የተገለጸው፡፡

በዚህም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ሶማሊና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ክትባቱ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በዚህ ዘመቻ ከአሁን በፊት የተከተቡ ህጻናት ጭምር ክትባቱን የሚወስዱ ሲሆን፥ ቤት ለቤት፣ በተፈናቃይና በስደተኛ ጣቢያዎች እንዲሁም በመግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ እንደሚሰጥ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

ፖሊዮን ጨርሶ ለማጥፋት ከተቀመጡ ስትራቴጂዎች መካከል የመደበኛ ክትባትን ማጠናከር አንዱ ሲሆን፥ መደበኛ ክትባት ያልጀመሩና ጀምረው ያቋረጡ ህጻናትን በመለየት የመከተብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ከክትባት ዘመቻው ጎን ለጎን የከንፈር እና የላንቃ የመሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን ልጆች የመለየትና ሕክምና እንዲያገኙ በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.