የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ባለሥልጣኑ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግና ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት የክትትል፣ የቁጥጥርና ድጋፍ ሥራውን ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን፡፡
ባለሥልጣኑ በማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ሀገራዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተከታይ ባላቸውና ከፍተኛ ይዘቶች በሚሰራጭባቸው አምስት የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች ማለትም ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ኤክስ እና ዩቲዩብ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
በመላ ሀገሪቱ ባሉ 5 ዋና ዋና ከተሞች እንዲሁም በ2ቱ ከተማ አስተዳደሮች ላይ በናሙና በተወሰደ የሕዝብ አስተያየትና በባለስልጣኑ የነፃ መስመር 9192 የቀረቡ ጥቆማዎች በግብዓትነት ጥቅም ላይ መዋላቸው ተመላክቷል።
ሪፖርቱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ እንዳሉት÷ ሪፖርቱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት የሚገኝበትን ሁኔታ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳየውን ለውጥና አሉታዊ ተፅዕኖ በማመላከት የመፍትሄ ሀሳብ ለመጠቆም ያለመ ነው፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዘው የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ ይዘቶች በሀገራችን ሰላም፣ ልማት፣ የዴሞክራሲ ግንባታ በቅርቡ በሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ስጋት እንዳይደቅኑ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ፕላትፎርም አገልግሎት ሰጪዎች በአዋጁ እንዲሁም በፕላትፎርሞቹ ደንብ እና መመሪያ መሰረት ግዴታ እና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የሕዝብን የመረጃ አጠቃቀም ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በቀጣይ በማናቸውም የማህበራዊ ትስስር ገጽ እና የዲጂታል ፕላትፎርሞች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ፣ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት በመገንባት እና ዘመናዊ የቁጥጥር፣ የክትትል እና የድጋፍ ሥርዓት በማጠናከር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን የመከላከል ስራ ለተወሰኑ ተቋማት ብቻ የተሰጠ ሃላፊነት ሳይሆን የሁሉንም ተቋማት እና ዜጎች ትብብር የሚጠይቅ ስለሆነ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመግታት በሚደረገው ሒደት ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት አመንጪዎችና ተጠቃሚዎች የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾችን ለህዝብ እና ለሀገር ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጡ በከፍተኛ ጥንቃቄ በኃላፊነትና ተጠያቂነት ስሜት እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡
በሲፈን መኮንን