በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2026 ፎረም ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 4ኛው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2026 ፎረም ዛሬ ተጠናቅቋል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ ዘርፎችን ያካተቱ በአጠቃላይ 13 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር የሚገመቱ የኢንቨስትመንት ውሎች ተፈርመዋል።
በፎረሙ መጨረሻ በተከናወነው የፊርማ መርሐ ግብር በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በኃይል፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች ትላልቅ የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ተፈርመዋል።
የተፈረሙት ውሎች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን የኢንቨስተሮች እምነት እንደሚያሳይ የተገለጸ ሲሆን፤ ውሎቹ ለስራ ፈጠራ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ እንደ ግንባር ቀደም የኢንቨስትመንት መዳረሻ እየታየች መሆኗን ያመላክታል ተብሏል።
ፎረሙ አዳዲስ አጋርነቶችን ለመፍጠርና ቀጣይ የኢንቨስትመንት ግንኙነቶችን ለማጎልበት ጠንካራ መድረክ መሆኑን መረጋገጡን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 ፎረም የተፈረሙ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት ውሎች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተዋል።