ምክር ቤቱ በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል የ10 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን ያስረከቡት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ እና የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ምህረቱ ሻንቆ (ዶ/ር) በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው÷ ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ወ/ሮ ሎሚ በዶ መሰል አደጋዎች ዳግም እንዳይከሰቱ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው÷ መንግሥት ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የምክር ቤቱ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የአደጋው መጠን ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማትና አጋር ድርጅቶች እያሳዩት ያለው አጋርነት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ላደረገው ድጋፍና ላሳየው አጋርነት ምስጋና በማቅረብ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም፣ መጠለያ ለመገንባት እና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ሁሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።