Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ ካልደረሰች ሙሉ ስልጣኔዋ ዛሬ ሌሊት ያበቃለታል ሲሉ አስጠነቀቁ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ዛሬ ሌሊት ሙሉ ሥልጣኔዋ በድጋሚ በማያንሠራራበት ሁኔታ ይወድማል አሉ፡፡

ኢራን ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጋር የገባችበትን ጦርነት ለማስቆም የቀረበውን ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ሃሳብ በዛሬው ዕለት ውድቅ ማድረጓ ይታወቃል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን የማትከፍት ከሆነ በሀገሪቱ የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ አስጠንቅቀው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ዛሬ ሌሊት ይጠናቀቃል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ኢራን ስምምነት ላይ በመድረስ የሆርሙዝ ወሽመጥን በድጋሚ ካልከፈተች አብዮታዊ ነገር ሊከሰት እንደሚችል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ቴህራን ስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ዛሬ ሌሊት ሙሉ ሥልጣኔዋ በድጋሚ በማይመለስበት ሁኔታ ይወድማል ሲሉ ነው ያስጠነቀቁት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ የኢራን ቁልፍ የነዳጅ ኤክስፖርት ተርሚናል በሆነው ካርግ ደሴት ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን መፈጸሟ ተሰምቷል፡፡

ከሰዓታት በፊት በካሻን ድልድይ ላይ በደረሰ ጥቃትም የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

የካርግ ደሴት የኢራን የኢኮኖሚ የሕይወት መስመር ተብሎ የሚታሰብ ዋና የነዳጅ ተርሚናል መገኛ ሲሆን÷ዶናልድ ትራምፕ ደሴቱን ለመቆጣጠር ወታደሮቻቸውን ሊልኩ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም ጠቁመው ነበር፡፡

በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር ኢራን በእስራኤል ላይ ተጨማሪ ሚሳኤሎችን እንዳስወነጨፈች አስታውቋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.