ከምን ጊዜም ምርጥ ተከላካዮች አንዱ ሮቤርቶ ካርሎስ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በግራ መስመር ተከላካይነት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ኮከብ ሮቤርቶ ካርሎስ፡፡
ብራዚላዊው የቀድሞ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ሮቤርቶ ካርሎስ ወደ ግብ በሚመታቸው ጠንካራ ኳሶች እና በሚያስቆጥራቸው የቅጣት ምት ግቦች በልዩነት ይታወቃል፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለቦች ሲሆን÷ በሪያል ማድሪድ ስኬታማ ዓመታትን አሳልፏል፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ በሎስብላንኮቹ ቤት ዚነዲን ዚዳን፣ ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ፣ ዴቪድ ቤካም እና ሉዊስ ፊጎ የነበሩበት የሪያል ማድሪድ ወርቃማው ስብስስብ አካል እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ በሪያል ማድሪድ በቆየባቸው 11 ዓመታት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕ እና የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን አሳክቷል፡፡
ተጫዋቹ ከተከላካይ ሥፍራ በመነሳት በሚያስቆጥራቸው አስደናቂ ግቦች እንዲሁም በቅጣት ምት ግቦቹ ሁሌም የሚታወስ ድንቅ ኮከብ ነው፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ ከማድሪድ በተጨማሪ ለኢንተር ሚላን፣ ፌነርባቼ፣ ኮረንቲያስ፣ አንዢ ማካቻካላ እና ፓልሜራስን ለመሳሰሉ ክለቦች ተጫውቷል፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ በእግር ኳስ ሕይወቱ በአጠቃላይ 1 ሺህ 100 ጨዋታዎችን አድርጎ 127 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ 49ኙ ግቦች ከቅጣት ምት የተገኙ ናቸው፡፡
ሀገሩ ብራዚልን ከፈረንጆቹ 1992 እስከ 2006 ያገለገለው ተጫዋቹ የዓለም ዋንጫ እና የኮፓ አሜሪካ ዋንጫዎችን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ማሳካቱ ይታወሳል፡፡
ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን 125 ጨዋታዎችን በማድረግ የብሔራዊ ቡድኑ 4ኛው በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገ ተጫዋች ሲሆን÷ የሚበለጠውም በካፉ፣ ኔይማር ጁኒየር እና ዳኒ አልቬስ ነው፡፡
በፈረንጆቹ 1997 በፊፋ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት እንዲሁም በፈረንጆቹ 2002 በባሎንዶር የሽልማት ሥነ ሥርዓት በተመሳሳይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2002 ከሀገሩ ብራዚል ጋር የዓለም ዋንጫ ማሳካት የቻለው ሮቤርቶ ካርሎስ÷ በወቅቱ የፊፋ የዓመቱ ምርጥ ስብስብ ውስጥ መካተቱ አይዘነጋም፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ በፈረንጆቹ 2012 ራሱን ከእግር ኳስ ዓለም ማግለሉን ቢያሳውቅም በድጋሚ ጫማውን በማውረድ ለሕንዱ ክለብ ዴሊ ዳይናሞስ ተጫውቶ በፈረንጆቹ 2015 ጫማውን መስቀሉን ይፋ አድርጓል፡፡
ጫማውን ከሰቀለ በኋላ ወደ አሰልጣኝነት በመግባት የቱርክ ክለብ የሆኑትን ሲቫስፖር እና አኪሳርስፖር እንዲሁም የህንዱን ዴሊ ዳይናሞስ በአሰልጣኝነት መምራት ችሏል፡፡
ሮቤርቶ ካርሎስ በአሁኑ ጊዜ በዋናነት የሪያል ማድሪድ ዓለም አቀፍ አምባሳደር ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡
ከምን ጊዜም ምርጥ ተከላካዮች አንዱ የሆነው ሮቤርቶ ካርሎስ በፈረንጆቹ 1973 በዛሬዋ ዕለት ነው የተወለደው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ