ፌዴሬሽኑ የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ በቅንጅት መስራት ይገባል አለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአካል ጉዳተኞች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሁሉም ሒደቶች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በትብብር መስራት ይገባል አለ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን፡፡
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳሉት ÷ የአካል ጉዳተኞች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና በድህረ ምርጫ ሒደት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
በቅድመ ምርጫ ሒደት ላይ የአካል ገዳተኞች የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በስፋት መከናወኑን አመልክተዋል፡፡
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምዝገባ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡
ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የምዝገባ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ከመሆን አንጻር ውስንነቶች እንዳሉባቸው አስረድተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአማራጭ ፖሊሲዎቻቸው ላይ አካል ጉዳተኞችን በበቂ ሁኔታ እያካተቱ አለመሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃን በሚሰሩት ዘገባ አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍ በምርጫው ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን ክርክር በሚያደርጉበት ወቅት አብዛኛዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የምልክት ቋንቋ እንደማይጠቀሙ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለማስተካከል እየተሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ÷ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን በሚገባ ሊወጡ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማት እየተካሄዱ ባሉ የቅድመ ምርጫ የውይይት ፕሮግራሞች እና ዘገባዎች አካል ጉዳተኞችን በተለይም መስማት የተሳናቸው ወገኖችን በሚፈለገው መጠን ማካተት አለባቸው ብለዋል፡፡
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት የምርጫ ጣቢያዎች፣ ቁሳቁሶችና መረጃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በእጩነት የመቅረብና ውሳኔ ሰጭ ቦታዎች ላይ የመድረስ እድል እንዲኖራቸው ማድረግ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡
በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለውን የግንዛቤ ችግር በመቅረፍ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አቶ አባይነህ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ