አየር መንገዱ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፕላን ክንፍ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፕላን ክንፍ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ አደረጉ።
ማሻሻያው የተደረገው አየር መንገዱ በሚያበራቸው የቦይንግ 767 አውሮፕላኖች ላይ መሆኑ ተጠቁሟል።
ይህ ማሻሻያም በዓመት እስከ 500 ሺህ ጋሎን ነዳጅ እንዲቆጥብ ያስችለዋል ነው የተባለው።
በተጨማሪ ማሻሻያው 277 ሺህ ሜትሪክ ቶን የካርበን ልቀትን የሚያስቀር በመሆኑ አየር መንገዱ በአካባቢ ጥበቃ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ተቋሙ አስታውቋል።
በማሻሻያው 69 የአየር መንገዱ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች ፕሮጀክቱን በስኬት አጠናቀዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎች ያከናወኑት የአውሮፕላን ክንፍ ላይ የምህንድስና ማሻሻያ በአፍሪካ አቪየሽን ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል መሆኑንም ከአየር መንገዱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።