ንቅናቄው ኢትዮጵያውያን ሲያመርቱ የተሻለ ውጤት መሆኑን የተማርንበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢትዮጵያ ስታመርት፣ ኢትዮጵያውያን ሲያመርቱ የተሻለ መሆኑን የተማርንበት ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል መሪ ሐሳብ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያመጣውን ውጤት በተመለከተ አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያሉ አቅሞችን በደንብ መንዝሮ ለመጠቀም፣ ክፍተቶቻችንን ለመለየት እና ተኪ ምርቶችን ለማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታዎችን በስፋት ለማምረት ያስቻለ ነው ብለዋል።
ኢንዱስትሪዎች እንዳያመርቱ ያገዳቸውን ችግር ለይቶ ለመደገፍ እና ኢትዮጵያውያን ኢንዱስትሪያሊስቶች እንዲበዙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እየመጣበት ያለ ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዚህም አሁን ላይ ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች 65 በመቶ የሚሆኑት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተሰማርተው ለወጪ ንግድ እና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህም ለቴክኖሎጂ ምርቶች ትኩረት በመስጠት እና ዕሴት የሚጨምሩ ምርቶችን በማሳደግ ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ለአብነትም ከሶላር ኃይል ማመንጫ ምርት ጋር በተያያዘ 13 ነጥብ 5 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል የሶላር ምርት እንደሚመረት ገልጸዋል።
እንዲሁም ከዚህ በፊት እየተመረተ ጥሬው ይሸጥ የነበረው የወርቅ ምርት በማዕድን ተኮር ፕሮጀክት ዕሴት የመጨመር ስራ ለመስራት የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ እየተገነባ መሆኑን እና በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚመረቅ ጠቁመዋል።
ፋብሪካው በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ያለውን ወርቅ ለመጠቀም የሚያግዝ እንደሆነ እና በቀላል ኢንቨስትመንት የሚሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ዕሴት በመጨመር ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ችግር የሚፈታ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
እንዲሁም በአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ እና በተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች እየተሰራ የሚገኘው ስራ ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር እንደሆነም አመላክተዋል።
በዮናስ ጌትነት