Fana: At a Speed of Life!

የኃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሀገሪቱን ሕጎች በማክበር ሊንቀሳቀሱ ይገባል – ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኃይማኖት መገናኛ ብዙኃን በኃይማኖቶች መካከል ግጭት ከሚቀሰቅሱና የሌሎችን እምነት ከሚያንኳስሱ ኃላፊነት የጎደላቸው ተግባራት ተቆጥበው የሀገሪቱን ሕጎች በማክበር ሊንቀሳቀሱ ይገባል አሉ የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳሬክተር ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ።
የኢትዮጵያን መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን “የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ለሰላምና ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል ከኃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የኃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች ተገኝተዋል።
ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ለህብረተሰቡና ለተከታዮቻቸው ኃይማኖታዊ አስተምህሯቸውን ከማድረስ ባሻገር አብሮነትን፣ መረዳዳትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ልማትን እና የጋራ ዕሴቶችን በማስረፅ አዎንታዊ አበርክቶ አላቸው።
ከሁሉም የኃይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተቋማቱ መገናኛ ብዙኃን በሕግ በተሰጣቸው ዕውቅና መሰረት ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ አስፈላጊውን የክትትልና ድጋፍ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በኃይማኖት ተቋማት መገናኛ ብዙኃን ላይ ላለፉት ሶስት ወራት ያካሄደውን የክትትልና የግምገማ ውጤት ሪፖርት በማቅረብ የጋራ የውይይት መድረኩን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሀፊና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የቦርድ አባል ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሰላምና አብሮነት የጎላ አበርክቶ አላቸው።
ኢትዮጵያ የበርካታ ኃይማኖት፣ የጥንታዊ ስልጣኔና የብዝሃ ማንነት ባለቤት መሆኗን ገልጸው፤ የኃይማኖት ተቋማት የዘመናት የሰላም ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ አመላክቷል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.