መካሄዱ ያልተረጋገጠው የአሜሪካና ኢራን 2ኛው ዙር የኢስላማድ ድርድር
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመካከለኛውን ምስራቅ ጦርነት ለመቋጨት በፓኪስታን አስተናጋጅነት ሊካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የአሜሪካ እና ኢራን 2ኛው ዙር ድርድር ስለመካሄዱ እስካሁን ርግጠኛ መሆን አልተቻለም።
የአሜሪካ ልዑካን ቡድንን የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ በድርድሩ ለመሳተፍ ወደ ኢስላማባድ ጉዞ መጀመራቸውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ ከኢራን በኩል በድርድሩ የሚሳተፍ ልዑክ እስካሁን ይፋ አለመደረጉንና በድርድሩ የመሳተፍ ዕቅድ አለመኖሩን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
ለዚህም የአሜሪካ ባሕር ኃይል በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ የኢራንን ሰንደቅ ዓላማ በምታውለበልብ መርከብ ላይ ተኩስ ከፍቶ በቁጥጥር ስር ማዋሉ እንደ ምክያንት ተጠቅሷል።
ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆይ የተገለጸው የሁለቱ ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት ረቡዕ ምሽት እንደሚያበቃና ተጨማሪ ማራዘሚያ የማይቻል መሆኑን ፕሬዚዳንት ትራምፕ መግለጻቸውን ያስነበበው ደግሞ ሲኤንኤን ነው።
አሜሪካ እና ኢራን ባደረጉት እና ያለ ውጤት በተበተነው የመጀመሪያ ዙር ንግግር ካላግባቧቸው ጉዳዮች አንዱ የቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ነው።
የኢራን ፕሬዚዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ሀገራቸው በአሜሪካ መንግሥት ላይ እምነት እንደሌላት ገልጸው÷ የተገቡ ቃሎችን ማክበር ትርጉም ላለው ውይይት መሠረት መሆን አለበት ብለዋል።
ከአሜሪካ ባለሥልጣናት የሚመጡ ገንቢ ያልሆኑ እና የሚቃረኑ ምልክቶች መራራ መልዕክት ያስተላልፋሉ፤ ኢራንም እጇን እንድትሰጥ ይፈልጋሉ ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በአድማሱ አራጋው