በቴክኖሎጂ የታገዘ የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋና አጠቃቀምን ለማጠናከር …
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘመኑን የዋጁ የጂኦ ፊዚካል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን በትክክል ለመለየትና ለመጠቀም እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታመነ ኃይሉ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ፥ የከርሰ ምድር ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የከርሰ ምድር ውሃ ፍለጋና አጠቃቀም በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የከርሰ ምድር ውሃን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችሉና ተደራሽነቱን የሚያጠናክሩ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ስኬት መጠን አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው ፥ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ዘመኑን የዋጁ የጂኦ ፊዚካል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ከዴንማርኩ ቲም ኩባንያ ጋር በዘርፉ ያለውን ቴክኖሎጂ ለማዘመን በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ጠቅሰዋል።
በስምምነቱ መሰረት ዘመናዊ የጂኦ ፊዚካል ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ እንደሚተገበሩና በዘርፉ የምርምር ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም በውሃ ጥራት፣ አቅርቦት እና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ በጋራና በቅንጅት እንደሚሰሩ ነው ያመለከቱት።
በተለይም በድርቅ ለሚጠቁ አካባቢዎች እና ለከተሞች የውሃ አቅርቦት ዋስትናን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ