Fana: At a Speed of Life!

24ኛው ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት የሚካሄደው የቁንጅና ውድድር ለ24ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ቁንጅና እና ውበት በሰብዓዊም ሆነ በመልክዓምድራዊ ገጽታ ኢትዮጵያን የሚገልጥ ሃብት ነው፡፡

መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ወግ፣ ባሕልና ሀገራዊ እሴት በልጆቿ እንዲገለጥ እና ለዓለም እንዲታይ እድል የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አዘጋጅነት ላለፉት 24 ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የቁንጅና ውድድር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ መልክ ለዓለም ማስተዋወቁን አውስተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው ሞዴል ሀሴት ደረጀን አስተዋፅኦ በማስታወስ ተወዳዳሪዎች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በ24ኛው የሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ 50 ቆነጃጅቶች የተሳተፉ ሲሆን÷ ራሳቸውን በመግለጽ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ 25 ተወዳዳሪዎች ተለይተዋል።

በውድድሩ ወ/ሪት ሩት ይርጋለም ኢትዮጵያን በዓለም የምትወክለዋ ቆንጆ ሆና በመመረጥ የ2026 ሚስ ወርልድ ኢትዮጵያ አሸናፊ የክብር ዘውድን መድፋት ችላለች።

ወ/ሪት ሩት በቀጣይ ኢትዮጵያን በመወከል በሚስ ወርልድ የዓለም ቁንጅና ውድድር ላይ የምትሳተፍ መሆኑንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.