በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተለዋዋጭ ተግዳሮቶችን ለመወጣት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወሳኝ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተለዋዋጭ ተግዳሮቶችን ለመወጣትና የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አቅም መጠቀም ወሳኝ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ከአፍሪካ በሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዣን ካሴያ ጋር በተለያዩ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤ አይ) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ በመሆን የተሰጠኝን አዲስ ኃላፊነት በሚመለከት በስፋት ተነጋግረናል ነው ያሉት።
በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ተለዋዋጭ ተግዳሮቶችን ለመወጣት፣ የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር፣ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና ለሕዝባችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አቅም መጠቀም ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ልምድ ለአህጉሩ ለማካፈል እንዲሁም በፍጥነት ከሚለዋወጠው የቴክኖሎጂው ዓለም ጋር ውጤታማ በሆነ መልኩ ለመራመድ የሚያስችሉ ጠንካራ አጋርነቶችን ለመመሥረት ቁርጠኛ መሆኗን በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
የፈጠራ ሥራዎች ለአፍሪካ ዕድገት ምንጊዜም ወሳኝ መሰረት መሆናቸውን ገልጸው፥ ይህንን ርዕይ ወደ ተጨባጭና አካታች ውጤት ለመለወጥ ከአፍሪካ ሲዲሲ እና በመላው አህጉሪቱ ከሚገኙ አጋሮች ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።