Fana: At a Speed of Life!

54 ቢሊየን ብር የሚገመቱ የመድሀኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት 54 ቢሊየን ብር ግምት ያላቸው የመድሀኒትና የህክምና ቁሳቁሶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል አሉ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናት እና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ በጤናው ዘርፍ የተመዘገበውን አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ተደራሽነትን፣ ጥራትንና ፍትሃዊነትን መሰረት በማድረግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

ከውጭ የሚገቡ መድሀኒቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረት ከሀገር ውስጥ የመድሀኒትና የህክምና ቁሳቁስ አምራቾች ጋር በርካታ ግዥዎች ተፈጽመዋል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 54 ቢሊየን ብር ወጭ በማድረግ መድሀኒቶችንና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ለተለያዩ ክልሎች ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በጤና ዘርፉ ዲጂታላይዜሽንን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ በተሰራው ስራ የጤና ተቋማት ያሉበትን ደረጃና የመድሃኒት አቅርቦት እንቅስቃሴዎችን መከታተል የሚያስችል ዲጂታል አሰራር ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን አንስተዋል፡፡

የጤና ዘርፉ በተለይም ህክምና ቁሳቁሶችንና መድሃኒቶችን በማምረት ኢንዱስትሪውን እየደገፈ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ዘርፉን በዲጂታል አሰራር የማዘመን የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን ውጤታማ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.