ኪነጥበብ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ያለውን ሚና የሚያጎሉ ሥራዎች ተከናውነዋል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኪነጥበብ ሥራዎች ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት እሴት ግንባታ የሚያበረክቱትን ሚና የሚያጎሉ ተግባራት ተከናውነዋል አሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፡፡
ሚኒስትሯ የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናትና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የኪነጥበብ ዘርፉን አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ከጥበብ ባለሙያዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ እየሰራ ሲሆን፥ የባህል ማዕከላትና የሲኒማ ቤቶች ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
በሀገሪቱ ያሉ ልዩ ልዩ የባህል ሀብቶች ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታና የዜጎችን ትስስር ለማጠናከር እንዲውሉ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፥ በዚህ ዓመት ብቻ 53 የተለያዩ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት በመላ ሀገሪቱ መከበራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ለአብነትም የተለያዩ ብሔሮች የዘመን መለወጫ በዓላት በሚከበሩበት ወቅት የሌሎች ብሔር ተወካዮች ጭምር ተገኝተው በጋራ ማክበራቸው ወንድማማችነትንና አንድነትን እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት፡፡
በተመሳሳይ ለስፖርቱ ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች የተገነቡ ሲሆን፥ እንደ አደይ አበባ ያሉ ስታዲየሞች ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በሚያሟላ መንገድ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ለአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው እድሳትና በአዲስ መልክ በተገነባው የመሮጫ መም ከወዲሁ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን መሳብ ተችሏል ነው ያሉት።
የስፖርት መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ሁነቶችን በማስተናገድ ረገድ ጥሩ ጅምር መኖሩንም አመልክተዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ