የታዳሽ ኃይል ፍላጎትን ለማሟላት…
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ባለፉት ዓመታት ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች።
በተለይም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የጀርባ አጥንት በሆነው የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ባከናወነችው ተግባር የተገኘው ውጤት እጅግ አመርቂ እየሆነ መጥቷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ በአብነት ሊጠቀሱ የሚችሉ የታዳሽ ኃይል ምንጭ የሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
ከእነዚህ መካከል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኦሞ ወንዝ ታችኛው ተፋሰስ ከጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ በ129 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው።
ፕሮጀክቱ 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን÷ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የኃይል ፍሰት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ የሆነው ይህ ፕሮጀክት÷ ንፁህ እና አስተማማኝ ታዳሽ ኃይል ያቀርባል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የኤሌክትሪክ የወጪ ንግድ ማዕከል ለመሆን ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካትም ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ይገላጻል።
በሀገር ውስጥም የገጠር ኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማሻሻል ልማትን የሚያነቃቃ፣ የተሻሻለ የአኗኗር ደረጃን የሚፈጥር ብሎም ዘላቂ እድገትን የሚደግፍ ይሆናል።