Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿን እንደ ስትራቴጂካዊ አጋር በመጠቀም ራሷን ማጠናከር ይኖርባታል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አዳም ተስፋዬ።

የአፍሪካ ዳያስፖራ ባለድርሻ አካላት መድረክ “የዳያስፖራ አቅም ለአህጉራዊ እድገት መጠቀምና ልምድ ልውውጥ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው።

አቶ አዳም ተስፋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አፍሪካ ፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥና ዓለም አቀፋዊ የሃብት ፉክክር ባለበት በዚህ ወቅት በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎቿን እንደ ስትራቴጂካዊ አጋር በመጠቀም ራሷን ማጠናከር ይኖርባታል።

ዳያስፖራው ለአህጉራዊ እድገት የጎላ ሚና መጫወት እንደሚችል እና ይህንን አቅም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማዕቀፎች መደገፍ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በተለይም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገቶች ላይ ዳያስፖራው ያለውን ክህሎትና ካፒታል ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ይህንን ራዕይ ወደ ተግባር ለመለወጥ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች ከዳያስፖራው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ለዳያስፖራው ሰፊ የኢንቨስትመንት እና የእውቀት ሽግግር እድሎችን እንደሚፈጥር ነው ያመላከቱት፡፡

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር መሀመድ ራፊ አባራያ በበኩላቸው÷ የአፍሪካ ዳያስፖራ ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር አህጉሪቱን የሚደግፍ ስትራቴጂካዊ አጋር ሆኗል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን ሰፊ አቅም በሙሉ አቅም ለመጠቀም የፖሊሲ ቅንጅት ማነስና የተቋማዊ አሰራር እንቅፋቶች አሁንም ተግዳሮት መሆናቸውን ጠቅሰው÷ መንግሥት ዳያስፖራውን እንደ ዋና የልማት አጋር የሚመለከት ዜጋ ተኮር አቀራረብ እየተከተለ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ዳያስፖራ በአህጉሪቱ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በእውቀት ሽግግር ከፍተኛ ሚና አለው፤ ዳያስፖራው ያለውን አቅም በሙሉ ደረጃ እንዳይጠቀም የመረጃ ተደራሽነት፣ የቅንጅት ማነስና የአሰራር እንቅፋቶችን መቅረፍ ይገባል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ናቸው።

በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የለውጥ ሥራዎች ለዳያስፖራው አዳዲስ የትስስር እድሎችን እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰው÷ ፎረሙ በፖሊሲ አውጪዎች፣ በግል ዘርፉና በዳያስፖራ ተወካዮች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ለአህጉራዊ እድገት የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል፡፡

በዘመን በየነ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.