Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ የኑክሌር ሚሳኤል ተሸካሚ አውሮፕላኖች ለሰዓታት የቆየ የቅኝት በረራ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ሚሳኤል ተሸካሚ አውሮፕላኖች በባሬንትስ እና ኖርዌይ ባህሮች ላይ ለሰባት ሰዓታት የቆየ የቅኝት በረራ አድርገዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ሁለት የሩሲያ ቲዩ-95ኤምኤስ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ሚሳኤል ተሸካሚ አውሮፕላኖች ገለልተኛ በሆነው የውሃ አካል ላይ ያደረጉት ለሰዓታት የቆየ በረራ ስኬታማ መሆኑን አስታውቋል።
የሩሲያ ኤሮስፔስ ኃይል የረጅም ርቀት አቪዬሽን አካል የሆኑት እነዚህ አውሮፕላኖች በረራውን ያካሄዱት በተያዘላቸው መርሐ ግብር መሰረት እንደሆነ ተገልጿል።
በበረራው ወቅት የአውሮፕላኑ አብራሪዎች በአየር ላይ ነዳጅ የመሙላት ልምምድ ያደረጉ ሲሆን፤ በኤስዩ-30ኤስኤም የጦር አውሮፕላኖችም እጀባ እንደተደረገላቸው ተጠቁሟል።
የሩሲያ ስትራቴጂካዊ የኒውክሌር ሚሳኤል ተሸካሚ አውሮፕላኖች በጉዟቸው ወቅት በተለያዩ መስመሮች ላይ የውጭ ሀገራት ተዋጊ ጄቶች ክትትል ሲያደርጉባቸው እንደነበርም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል።
የሀገሪቱ አየር ኃይል የሚያደርጋቸው ማናቸውም በረራዎች ዓለም አቀፍ የአየር ክልል አጠቃቀም ደንቦችን በጥብቅ የተከተሉ ናቸው ሲልም አረጋግጧል።
የሩሲያ የረጅም ርቀት አቪዬሽን ቡድኖች በአርክቲክ፣ በሰሜን አትላንቲክ፣ በፓስፊክ ውቅያኖስ፣ በባልቲክ እና ጥቁር ባሕር ገለልተኛ ውሃዎች ላይ በየጊዜው ተመሳሳይ በረራዎችን እንደሚያደርጉ የአናዶሉ ዘገባ ያመላክታል።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.