የቀድሞ ብቃቱ ላይ የማይገኘው ቡካዮ ሳካ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት ለአርሰናል የዋንጫ ተፎካካሪነት ትልቁን ሚና መወጣት የቻለ ተጫዋች ነው ቡካዮ ሳካ፡፡
በፈረንጆቹ 2001 የተወለደው ቡካዮ ሳካ የአርሰናል አካዳሚን የተቀላቀለው ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ ነበር፡፡
ቡካዮ ሳካ ፕሮፌሽናል ኮንትራቱን በፈረንጆቹ 2010 የተፈራረመ ሲሆን በ17 ዓመቱ ለአርሰናል ዋናው ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ አድርጓል፡፡
እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ቡካዮ ሳካ ባለፉት ዓመታት በሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል አይነኬ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አርሰናል ወደ አውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ሲመለስ እና ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመታት በሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ትልቁን አስተዋጽኦ ካበረከቱ ተጫዋቾች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
ሳካ ምርጥ በነበረባቸው ያለፉት ዓመታት ልዩነት ፈጣሪነቱ እና ጨዋታ የማንበብ ብቃቱ ልዩ ነበር፡፡
ገና በወጣትነቱ የአርሰናል የማይነካ ተጫዋች መሆን የቻለው ቡካዮ ሳካ ለቡድን አጋሮቹ ጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ የማቀብል ችሎታው ድንቅ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አርሰናል ጥሩ ባልሆነባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ቡካዮ ሳካ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡
ቡካዮ ሳካ ምርጥ በነበረባቸው ባለፉት ዓመታት በተከታታይ በ2020/21 እና በ2021/22 የውድድር ዓመት የአርሰናል የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡
በ2022/23 የውድድር ዓመት 27 የግብ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን በ2023/24 ደግሞ 34 የግብ ተሳትፎ እንደነበረው ይታወሳል፡፡
ሳካ በነበረው ፈጣን ዕድገት ለእንግሊዝ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በ19 ዓመቱ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ መጫወት ችሏል፡፡
ሳካ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ውድድሮች ለአርሰናል በርካታ ጨዋታዎችን በማድረጉ ለድካም እና ላልተፈለገ ጉዳት እንዳይጋለጥ የብዙዎች ስጋት ነበር፡፡
ተጫዋቹ የተፈራው ጉዳት ካጋጠመው በኋላ በዚህ የውድድር ዓመት የቀድሞ ብቃቱን በድጋሚ ማሳየት አልቻለም፡፡
ከ2024/25 የውድድር ዓመት ጀምሮ ቡካዮ ሳካ በጉዳት እየተፈተነ ይገኛል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት በፈረንጆቹ መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ ጉዳት አጋጥሞት የነበረው ቡካዮ ሳካ ወደ ሜዳ የተመለሰው በሳምንቱ መጨረሻ ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር በተደረገው ጨዋታ ሲሆን ተቀይሮ ገብቶ መጫወት ችሏል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ደግሞ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በተደረገው ጨዋታ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሳካ የቀድሞ ብቃቱን ሜዳ ላይ ለማሳየት ተቸግሯል፡፡
የ24 ዓመቱ ተጫዋች ቡካዮ ሳካ በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ 28 ጨዋታዎችን ማድረግ ቢችልም 6 ግቦችን ብቻ አስቆጥሮ ሦስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ነው አመቻችቶ ያቀበለው፡፡
በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ባደረጋቸው 9 ጨዋታዎች ደግሞ ሁለት ግብ አስቆጥሮ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ባለፉት ዓመታት ለተከላካዮች ፈታኝ የነበረው ተጫዋቹ በዚህ የውድድር ዓመት ወደ ሜዳ ገብቶ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ያንን ለማድረግ እየተቸገረ ይገኛል፡፡
ግብ በማስቆጠር እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ረገድም ደካማ እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል፡፡
ባለፉት ዓመታት በርካታ የግብ እድሎችን ሲፈጥር እና ግቦችን ሲያስቆጥር የነበረው ቡካዮ ሳካ አሁን ያንን እያደረገ አይገኝም፡፡
አርሰናል ያለፉትን ዓመታት በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለዋንጫ እንዲፎካከር ትልቁን ሚና ሲወጣ የነበረው ሳካ ጉዳት በተደጋጋሚ እየፈተነው የቀድሞ ብቃቱን መልሶ ለማግኘት ተቸግሯል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ